News News

በባህርዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ የግንባታ ስራ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡

በባህርዳር ከተማ  እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ የግንባታ ስራ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱን የስራ እንቅስቃሴ እና  የባህርዳር ጢስ እሳት የመንገድ ግንባታ  ስራን   በትራንስፖርት ሚኒስትር ድኤታው  አቶ ካሳሁን ጎፌ ፣በኢመባ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኘ እና የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በመስክ የስራ ቅኘት ተጎብኝቷል።አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ 380 ሜትር ርዝመት እና  43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ድልድይ ነው።በጉብኝቱ ወቅት ፕሮጀክቱ ላይ በዋነኛነት የድልድይ ተሸካሚ ምሰሶዎችን (piers) ለአርማታ ሙሌት ስራ ማመቻቸት  እንዲሁም የድጋፍ ግንቡን ከመሬት በታች የድልድዩ የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች (Abutment piles) ቁፋሮ እና አርማታ ሙሌት ስራ ነው እየተከናወነ የሚገኘው፡፡ለድልድዩ ከሚያስፈልጉት 4 ቋሚ የድልድይ ተሸካሚ ምሶሶውች የመሰረት ስራቸው ከነ ማቀፊያው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል፡፡  በተጨማሪም የአንዱ ድልድይ ተሸካሚ ምሶሶ የኮንክሪት ሙሌት ስራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የቀሪዎቹ ሶስት  ድልድይ ተሸካሚ ምሶሶ ሙሌት ስራም በመጪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡ 

ከመሬት በታች የሚቀበሩት  የክብ ቅርፅ ያላቸው የድልድዩ የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች  በዲዛይኑ መሰረት ከዝቅተኛው 14 ሜትር እስከ ከፍተኛው 23 ሜትር ድረስ ጥልቀት ያላቸው ሲሆኑ የአንዱ የቋሚ ተሸካሚ መሰረት የመሀል መለኪያ ስፋት በድልድዩ የድጋፍ ግንብ ጋር 1.5 ሜትር ሲሆን የመካከል ተሸካሚዎች ጋር ደግሞ 1.8 ሜትር ነው፡፡ 380 ሜትር የሚረዝመው አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ የግንባታ ስራ ፕሮጀክት በእስካሁኑ አፈፃፀም በአጠቃላይ ድልድዩን ለመሸከም ከሚያስፈልጉ 88  የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች ውስጥ 54 የሚሆኑት የቁፋሮ እና የአርማታ ሙሌት ስራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ የቀሪዎቹን የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶችም በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡የድልድዩ ስራ  አሁናዊ የግንባታ ስራዎች  አራት ቋሚ ተሸካሚ ምሶሶዎች  የኮንክሪት ሙሌት እና የብርት ማሰር ስራዎች ተከናውነዋል።የድልድዩን ዋና ዋና ስራዎችን በእቅዱ መሰረት ለማከናወን አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ በመፍጠን ላይ መሆኑ በስራ ሃላፊዎቹ ተገምግሟል።

የስራ ሃላፊዎቹ በቀጣይ የሚጠበቁ ጉልህ ስራዎችን ኮንትራክተሩ በገባው ውል መሰረት በጥራት እንዲሰራም ቀጣይ የስራ አቅጣጫን ሰተዋል።ድልድዩ  በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ 6 ተሽከርካሪዎችን በተጨማሪም 5 ሜትር የእግረኛ መንገድ እንዲሁም የብስክሌት ተጠቃሚዎችን መስመር ባካተተ መልኩ ነው እየተገነባ የሚገኘው ፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ 1.4 ቢሊዮን ብር ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው   ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ  የተባለው  ተቋራጭ ነው።በባህር ዳር ከተማ ከሚገኘው ነባሩ የአባይ ወንዝ ድልድይ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተገነባ ያለው ይህ ዘመናዊ ድልድይ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ከሚያበረክተው  ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ጎን ለጎን ምቹ የሆነ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር በማድረግና መስመሩን ከአደጋ የፀዳ እንዲሆን ከማስቻሉ ባሻገር ከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንድትላበስ ብሎም የሀገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋዕፆ ያበረክታል፡፡በተያያዘ ዜናም የስራ ሃላፊዎቹ በዛሬው የመስክ ጉዞቸው የባህርዳር ጢስ እሳት መንገድ ፕሮጀክትን ቃኝተዋል ።ፕሮጀክቱ ወደ ጢስ አባይ  ፏፏቴ ቱሪስት  መዳረሻ  የሚወስድ ሲሆን 22.3 ኪሎሜትር እርዝመት ያለው ነው።የዚህ መንገድ መገንባት  የሀገር ውስጥና  የውጪ ሀገር  ጎብኚዎች ከዚህ ቀደም ይፈጠርባቸው የነበረውን እንግልት በማስቀረት  ለአካባቢውም ሆነ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭን ይፈጥራል፡፡የመስክ ቅኝቱ  በዋነኝነት የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ለመገምገምና  እና በግንባታ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ  ከወሰን ማስከበር እና ተያያዥ ችግሮችን እየቀረፉ የግንባታ ስራቸውን ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ለመምከር ነው።